10 መልእክተኞቹም በኤፍሬምና በምናሴ ምድር ካንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመዘዋወር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ ሕዝቡ ግን አንቋሸሻቸው፤ ተሣለቀባቸውም።
11 ሆኖም ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
12 እንዲሁም ንጉሡና ሹማምቱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ያዘዙትን እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ነበር።
13 በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ።
14 በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎች ነቃቅለው፣ የዕጣን መሠዊያዎችንም ከስፍራው አንሥተው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣሉ።
15 በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ስለ ነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመጡ።
16 ከዚያም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደታዘዘው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ። ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።