1 ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ፣ በዚያ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው፣ የማምለኪያ ድንጋዮችን ሰባበሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶች ቈረጡ፤ እንዲሁም በመላው ይሁዳና በብንያም፣ በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኰረብታ መስገጃዎችና መሠዊያዎች አጠፉ፤ እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ካጠፉ በኋላ ወደየከተሞቻቸውና ወደየርስታቸው ተመለሱ።
2 ሕዝቅያስ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ እንዲያገለግሉና እንዲያመሰግኑ እንዲሁም በእግዚአብሔር ማደሪያ ደጆች ውዳሴውን እንዲዘምሩ፣ ካህናትንም ሆኑ ሌዋውያንን እያንዳንዳቸውን እንደየተግባራቸው በየክፍሉ መደባቸው።
3 በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ንጉሡ ጠዋትና ማታ እንደዚሁም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻውና በተወሰኑ በዓላት፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከራሱ ንብረት ሰጠ።
4 ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜአቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ።