2 ዜና መዋዕል 31:4-10 NASV

4 ካህናቱና ሌዋውያኑም ሙሉ ጊዜአቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጣቸው አዘዘ።

5 ትእዛዙ እንደ ወጣ እስራኤላውያን ወዲያውኑ የእህሉንና የአዲሱን ወይን ጠጅ፣ የዘይቱንና የማሩን እንዲሁም የዕርሻውን ፍሬ ሁሉ በኵራት በልግሥና ሰጡ፤ ካላቸው ከማንኛውም ነገር ሁሉ ላይ እጅግ ብዙ የሆነ ዐሥራት አውጥተው አመጡ።

6 በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ከከብቶቻቸው፣ ከበግና ከፍየል መንጎቻቸውና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ከለዩአቸው የተቀደሱ ነገሮች ዐሥራት አውጥተው አመጡ፤ ከመሩትም።

7 ይህንም በሦስተኛው ወር ጀምረው፣ በሰባተኛው ወር አጠናቀቁ።

8 ሕዝቅያስና ሹማምቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።

9 ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቃቸው፤

10 ከሳዶቅ ቤተ ሰብ የሆነው ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስም፣ “ሕዝቡ ስጦታውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማምጣት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በቂ ምግብ አግኝተናል፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለባረከም ይህን ያህል ብዛት ያለው ሊተርፍ ችሎአል” አለ።