2 ዜና መዋዕል 32:13-19 NASV

13 “እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ የእነዚያ መንግሥታት አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን?

14 አባቶቼ ካጠፏቸው ከእነዚህ የመንግሥታት አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን የቻለ ከእነዚህ አምላክ የትኛው ነው? ታዲያ አምላካችሁ እንዴት ከእጄ ሊያድናችሁ ይችላል?

15 አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ ዐይነት አያታልላችሁ፤ አያስታችሁም። የየትኛውም አገር ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ መታደግ የቻለ ስለሌለ አትመኑት። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!”

16 የሰናክሬም ሹማምትም በእግዚአብሔር አምላክና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ተናገሩ።

17 ንጉሡም እንደዚሁ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በመሳደብ፣ “የሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች አማልክት፣ ከእጄ እንዳልታደጉ ሁሉ፣ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም” ሲል በእርሱ ላይ ደብዳቤ ጻፈ።

18 ከዚያም በማስደንገጥና በማስፈራራት ከተማዪቱን ለመያዝ ሲሉ በቅጥሩ ላይ ወደተቀመጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በዕብራይስጥ ቋንቋ ጮኹ፤

19 የሰው እጅ በሠራቸው በሌሎች የምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደ ተናገሩት ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ።