14 ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።
15 ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።
16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤
17 በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”
18 ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።
19 ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
20 እርሱም ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም፣ ለሚክያስ ልጅ ለዓብዶን፣ ለጸሓፊው ለሳፋንና ለንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለዓሳያ ይህን ትእዛዝ ሰጠ፤