2 ዜና መዋዕል 34:17-23 NASV

17 በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”

18 ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።

19 ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።

20 እርሱም ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም፣ ለሚክያስ ልጅ ለዓብዶን፣ ለጸሓፊው ለሳፋንና ለንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለዓሳያ ይህን ትእዛዝ ሰጠ፤

21 “ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ቅሬታዎች በተገኘው መጽሓፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቊጣ ፈስሶአል፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”

22 ኬልቅያስና ንጉሡ ከእርሱ ጋር የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍለ ከተማ ትኖር ነበር።

23 ነቢይቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤