2 ዜና መዋዕል 35:18-24 NASV

18 ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።

19 ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንኛው ዓመት ነበር።

20 ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አደራጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ፣ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ።

21 ኒካዑ ግን፣ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተንና እኔን የሚያጣላን ምንድ ነው? ጦርነት ከገጠምሁት ቤት ጋር እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንተን የምወጋህ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር እንድፈጥን አዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ያለውን እግዚአብሔርን መቃወምህን ተው፤ ያለዚያ ያጠፋሃል” አለው።

22 ኢዮስያስ ግን ሌላ ሰው መስሎ በጦርነት ሊገጥመው ወጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተመለሰም፤ በመጊዶ ሜዳ ላይ ሊዋጋው ሄደ እንጂ ኒካዑ ከእግዚአብሔር ታዞ የነገረውን ሊሰማ አልፈለገም።

23 ቀስተኞች ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ እርሱም የጦር መኮንኖቹን፣ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከዚህ አውጡኝ” አላቸው።

24 ስለዚህ ከሠረገላው አውርደው በራሱ ሠረገላ ላይ አስቀምጠውት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ እዚያም ሞተ፤ በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ አለቀሱለት።