2 ዜና መዋዕል 36:12-18 NASV

12 እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።

13 እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።

14 ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለ መታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።

15 የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤

16 እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።

17 ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደናፆር አሳልፎ ሰጠው።

18 እርሱም ትልልቁንም ሆነ ትንንሹን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ በሙሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሀብት፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።