2 ዜና መዋዕል 36:19-23 NASV

19 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን በሙሉ አቃጠሉ፤ በዚያ የነበረውንም የከበረ ዕቃ በሙሉ አጠፉ።

20 ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።

21 ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።

22 በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት፣ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

23 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤“ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ በመካከላችሁ የሚገኝ ማናቸውም ሰው፣ እግዚአብሔር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ወደዚያው ይውጣ።’ ”