2 ዜና መዋዕል 5:10-14 NASV

10 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ከእነርሱ ጋር ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።

11 ካህናቱም ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እዚያ የነበሩት ካህናት በምድባቸው መሰረት ባይሆንም፣ ሁሉም ራሳቸውን ቀድሰው ነበር።

12 መዘምራን የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፣ አሳፍ፣ ኤማን፣ ሄማንና ኤዶታም፣ ወንዶች ልጆቻቸውና የሥጋ ዘመዶቻቸው ሁሉ ያማረ ቀጭን በፍታ ለብሰው፣ ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ በኩል ቆመው ጸናጽል ይጸነጽሉ፣ በገና ይደረድሩና መሰንቆ ይመቱ ነበር፤ እነርሱም መለከት በሚነፉ አንድ መቶ ሃያ ካህናት ታጅበው ነበር።

13 መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣“እርሱ ቸር ነው፣ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”እያሉ ዘመሩ።ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ።

14 የእግዚአብሔር ክብር የአምላክን ቤተ መቅደስ ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም።