14 እንዲህም አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋር የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤
15 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።
16 “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ከቶ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት።
17 እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።
18 “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!
19 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ።
20 ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዓይኖችህ በቀንም በሌሊትም የተገለጡ ይሁኑ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ።