2 ዜና መዋዕል 7:14-20 NASV

14 በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።

15 አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ።

16 ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሸዋለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።

17 “አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕግጋቴን ብትጠብቅ፣

18 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘ከዘርህ እስራኤልን የሚገዛ አታጣም’ ብዬ በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።

19 “እናንተ ግን እኔን ከመከተል ተመልሳችሁ የሰጠኋችሁን ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትተው፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኩ፣

20 በዚያን ጊዜ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፤ በሕዝቦችም ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ አደርገዋለሁ።