4 ለእግዚአብሔር ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሰነፎች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም።
5 ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል።
6 አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። እግዚአብሔር በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?
7 ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ።
8 በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ።
9 ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም ነው፤ ንጉሡም ራሱ የሚጠቀመው ከዕርሻ ነው።
10 ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ይህም ከንቱ ነው።