1 ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤
2 ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤
3 ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም ጊዜ አለው፤ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤
4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤
5 ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው፤
6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው፤ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤
7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤
8 ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው።
9 ሠራተኛ ከጥረቱ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?
10 ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ።
11 ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።
12 ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ።
13 ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።
14 እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከእርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ያከብሩት ዘንድ ይህን አደረገ።
15 አሁን ያለው ከዚህ በፊት የነበረው ነው፤ወደ ፊት የሚሆነውም ቀድሞ የነበረ ነው፤እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።
16 ከፀሓይ በታችም ሌላ ነገር አየሁ፤በፍርድ ቦታ ዐመፅ ነበር፤በፍትሕ ቦታ ግፍ ነበር።
17 እኔም በልቤ“ለማንኛውም ድርጊት፣ለማንኛውም ተግባር ጊዜ ስላለው፣እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጢአተኛውን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል”ብዬ አሰብሁ።
18 እንዲህም ብዬ አሰብሁ፤ “ሰዎች፣ እንደ እንስሳት መሆናቸውን ያዩ ዘንድ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል።
19 የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው፤ አንዱ እንደሚሞት፣ ሌላውም እንዲሁ ይሞታል። ሁሉ አንድ ዐይነት እስትንፋስ አላቸው፤ ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነው።
20 ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ሁሉም ከዐፈር እንደሆኑ፣ ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ።
21 የሰው መንፈስ ወደ ላይ መውጣቱን፣ የእንስሳ እስትንፋስ ደግሞ ወደ ታች ወደ ምድር መውረዱን ማን ያውቃል?”
22 ስለዚህ ለሰው ዕጣ ፈንታው ስለ ሆነ፣ በሥራው ከመደሰት የተሻለ ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ተመልሶ እንዲያይ የሚያደርገው ማን ነው?