መክብብ 7 NASV

ጥበብ

1 መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል።

2 ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።

3 ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና።

4 የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።

5 የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል።

6 የሰነፎች ሣቅ፣ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

7 ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤ጒቦም ልብን ያበላሻል።

8 የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል፤

9 የሞኞች ቊጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣በመንፈስህ ለቊጣ አትቸኵል።

10 አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።

11 ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።

12 ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ሁሉ፣ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።

13 እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤እርሱ ያጣመመውን፣ማን ሊያቃናው ይችላል?

14 ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን አስብ፤እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣ሌላውንም አድርጎአል፤ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ምንም ሊያውቅ አይችልም።

15 በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም።

16 እጅግ ጻድቅ፣እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ራስህን ለምን ታጠፋለህ?

17 እጅግ ክፉ አትሁን፤ሞኝም አትሁን፤ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ?

18 አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውጽንፈኝነትን ያስወግዳል።

19 በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች።

20 ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።

21 የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤አለበለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤

22 ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና።

23 እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣“ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር።

24 ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤ማንስ ሊደርስበት ይችላል?

25 ስለዚህ ጥበብንና የነገሮችን አሠራር ለመመርመርና ለማጥናት፣የክፋትን መጥፎነት፣የሞኝነትንም እብደት ለማስተዋል፣አእምሮዬን መለስሁ።

26 ልቧ ወጥመድ፣እጆቿም እግር ብረት የሆኑ፣አሽክላ የሆነች፣ከሞት የከፋችዋን ሴት አገኘሁ፤እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከእጇ ያመልጣል፤ኀጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች።

27 ሰባኪው እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው፤“የነገሮችን ብልኀት መርምሮ ለማግኘት፣አንዱን በአንዱ ላይ በመጨመር፣

28 ገና በመመርመር ላይ ሳለሁ፣ግን ያላገኘሁት፣ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12