ሚልክያስ 3:1-7 NASV

1 “እነሆ፤ በፊቴ መንገድ እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

2 እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ አጣቢ ሳሙና ነውና።

3 ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቊርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤

4 በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቊርባን እንዳለፉት ቀናትና እንደ ቀድሞው ዘመን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።

5 “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

6 “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።

7 ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዛቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።“እናንተ ግን፣ የምንመለሰው እንዴት ነው ትላላችሁ?”