ሶፎንያስ 3:7-13 NASV

7 እኔም ከተማዪቱን፣‘በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፤ዕርምትም ትቀበያለሽ’ አልኋት፤ስለዚህ መኖሪያዋ አይጠፋም፤ቅጣቴም ሁሉ በእርሷ ላይ አይደርስም።እነርሱ ግን በሚያደርጉት ሁሉ፣ክፋትንም በመፈጸም እየተጉ ሄዱ።

8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስጠብቁኝ፤አሕዛብን ላከማች፣መንግሥታትን ልሰበስብ፣መዓቴንና ጽኑ ቊጣዬን፣በላያቸው ላፈስ ወስኛለሁ፤በቅናቴ ቍጣ እሳት፣መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።

9 “በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም እንዲጠሩ፣ተስማምተው እንዲያገለግሉት፣አንደበታቸውን አጠራለሁ።

10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ፣የሚያመልኩኝ፣ የተበተኑት ሕዝቤቊርባን ያመጡልኛል።

11 በእኔ ላይ ከፈጸማችሁት በደል ሁሉ የተነሣ፣በዚያ ቀን አታፍሩም፤በትዕቢታቸው የሚደሰቱትን፣ከዚህች ከተማ አስወግዳለሁና፤ከእንግዲህ ወዲያ፣በቅዱስ ተራራዬ ላይ አትታበዩብኝም።

12 በእግዚአብሔር ስም የሚታመኑትን፣የዋሃንንና ትሑታንን፣በመካከላችሁ አስቀራለሁ።

13 የእስራኤል ትሩፋን ኀጢአት አይሠሩም፤ሐሰትም አይናገሩም፤በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም።ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤የሚያስፈራቸውም የለም።