አስቴር 7:1-6 NASV

1 ስለዚህ ንጉሡና ሐማ ከንግሥት አስቴር ጋር ለመጋበዝ ሄዱ፤

2 በሁለተኛውም ቀን የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ፣ ንጉሡ እንደ ገና፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል” አላት።

3 ከዚያም ንግሥት አስቴር እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው።

4 እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለዕርድና ለመደምሰስ ተሸጠናልና። ወንዶችና ሴቶች ባሮች ለመሆን የተሸጥን ቢሆን ኖሮ፣ ዝም ባልሁ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ጭንቀት ንጉሡን ለማስቸገር የሚበቃ አይደለም።”

5 ንጉሥ ጠረክሲስም ንግሥት አስቴርን፣ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ።

6 አስቴርም፣ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች።ከዚያም ሐማ በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት እጅግ ደነገጠ።