ዕዝራ 1:1-6 NASV

1 ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት፣ እግዚአብሔር የቂሮስን መንፈስ አነሣሥቶ በመንግሥቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፤ ይህ የሆነው በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

2 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የሚለው ይህ ነው፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ለእርሱ ቤተ መቅደስ እንድሠራ አዞኛል።

3 ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚኖር ማናቸውም ሰው አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ፤

4 ባሉበት ስፍራ የሚቀሩ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ እንዲሆን በበጎ ፈቃድ ከሚያቀርቡት መባ በተጨማሪ ብርና ወርቅ፣ ዕቃና እንስሳ በመስጠት ይርዷቸው።’ ”

5 ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም ቤተ ሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ተዘጋጁ።

6 ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በበጎ ፈቃድ ከሰጡት መባ በተጨማሪ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፣ ቈሳቍስን፣ እንስሶችንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችንም በመለገስ ረዷቸው።