11 እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት።
12 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “እግዚአብሔር ጸባኦት ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ።
13 እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።
14 ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤
15 ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’
16 “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።’
17 “ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”