ዘካርያስ 12:5-11 NASV

5 የይሁዳ መሪዎች በልባቸው፣ ‘የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ብርቱ ናቸው፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ጸባኦት ነውና’ ይላሉ።

6 “በዚያ ቀን የይሁዳን መሪዎች በዕንጨት ክምር ውስጥ እንዳለ የእሳት ምድጃ፣ በነዶም መካከል እንዳለ የፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በግራና በቀኝ ዙሪያውን ያሉትን ሕዝቦች ይበላሉ፤ ኢየሩሳሌም ግን ከስፍራዋ ንቅንቅ አትልም።

7 “የዳዊት ቤትና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከይሁዳ ክብር እንዳይበልጥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የይሁዳን መኖሪያዎች ያድናል።

8 ከመካከላቸው እጅግ ደካማ የሆነው እንደ ዳዊት፣ የዳዊት ቤትምፊት ፊታቸው እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንደ አምላክ ይሆንላቸው ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እግዚአብሔር ይከልላቸዋል።

9 በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን በወጓት አሕዛብ ሁሉ ላይ እወጣለሁ።

10 “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የልመና መንፈስ አፈሳለሁ፤ ወደ ወጉኝ ወደ እኔም ይመለከታሉ፤ እነርሱም ለአንድያ ልጅ እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኵር ልጅ ምርር ተብሎ እንደሚለቀስም አምርረው ያለቅሱለታል።”

11 በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ ለሐዳድሪሞን እንደተለቀሰ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚለቀሰውም እንደዚሁ ታላቅ ልቅሶ ይሆናል።