ዘካርያስ 14:2-8 NASV

2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም።

3 እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚ ዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።

4 በዚያን ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤

5 እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅሆሳኑም ሁሉ አብረውት ይመጣሉ።

6 በዚያ ቀን በረዶ ውርጭና ብርሃን አይኖርም።

7 ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።

8 በዚያን ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።