34 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤
35 “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤
36 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።”
37 በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም።
38 ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ፣ አበረታታው።
39 ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል።
40 እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።”