ዘዳግም 10:3-9 NASV

3 ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።

4 እግዚአብሔር (ያህዌ) በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፎአቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዛት በእነዚህ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።

5 ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቶቹን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።

6 እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔያዕቃን፣ የያዕቃን ልጆች ከቈፈሯቸው የውሃ ጒድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛር በእርሱ ምትክ ካህን ሆነ።

7 ከዚያም ተነሥተው ጒድጎዳ ወደተባለ ስፍራ፣ ቀጥሎም የውሃ ፈሳሾች ወዳሉባት ዮጥባታ ወደምትባል ምድር ተጓዙ።

8 በዚያን ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሌዊን ነገድ ለየ።

9 ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።