ዘዳግም 13:1-7 NASV

1 ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ከመካከልህ ተነሥቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ፣

2 የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፣ “አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው” ቢልህ፣

3 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወዱት እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ሊፈትናችሁ ነውና፣ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም ዐላሚውን አትስማ።

4 አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተከተሉት፤ ፍሩት፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ታዘዙት፤ አገልግሉት፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።

5 ከግብፅ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ላይ እንድታምፁ ተናግሮአልና፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጎአልና፣ ያ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።

6 የእናትህ ልጅ ወንድምህ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወይም የምትወዳት ሚስትህ ወይም የልብ ጓደኛህ፣ “ሄደን ሌሎችን አማልክት እናምልክ” (አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን አማልክት፣) ብሎ በስውር ሊያስትህ ቢሞክር፣

7 በቅርብም ሆነ በሩቅ፣ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላው ድረስ በዙሪያህ ያሉትን የአሕዛብ አማልክት እናምልክ ቢልህ፣