ዘዳግም 18:12-18 NASV

12 እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ነውና፣ ከእነዚህ አጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።

13 በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ነውር አልባ ሁን።

14 ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልፈቀደልህም።

15 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱን አድምጥ።

16 በኮሬብ ጉባኤ በተደረገበት ዕለት፣ “እንዳልሞት የአምላክህ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ አልስማ፤ እንዲህ ያለውንም አስፈሪ እሳት ደግሜ አልይ” ብለህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ያህዌ ኤሎሂም) የጠየቅኸው ይህን ነውና።

17 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “የተናገሩት መልካም ነው፤

18 ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌን በአፉ አደርጋለሁ፤ የማዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል።