ዘዳግም 2:1-7 NASV

1 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ተንከራተትን።

2 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

3 “በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ።

4 ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ።

5 ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታህል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሷቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ።

6 ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጒዞ ጠብቆአችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።