ዘዳግም 2:4-10 NASV

4 ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ።

5 ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታህል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሷቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ።

6 ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጒዞ ጠብቆአችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

8 ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞአብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን።

9 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሷቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ።

10 በዚያም ጠንካራና ቊጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረጃጅም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር።