ዘዳግም 2:6-12 NASV

6 ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጒዞ ጠብቆአችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

8 ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞአብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን።

9 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሷቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ።

10 በዚያም ጠንካራና ቊጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረጃጅም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር።

11 እነዚህም እንደ ዔናቃውያን ሁሉ ራፋይማውያን ናቸው ተብለው ይገመቱ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሯቸዋል።

12 ሖራውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።