1 ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብፅ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ ጋር ነውና።
2 ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤
3 እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤
4 ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ አብሮአችሁ የሚወጣው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነውና።”