ዘዳግም 20:1-7 NASV

1 ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብፅ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ ጋር ነውና።

2 ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤

3 እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤

4 ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ አብሮአችሁ የሚወጣው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነውና።”

5 አለቆቹም ለሰራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል።

6 ወይን ተክሎ ገና ያልበላለት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ወይኑን ሌላ ሰው ይበላዋል።

7 ሚስት አጭቶ ያላገባት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ይሞትና ሌላ ሰው ያገባታል።”