ዘዳግም 21:11-17 NASV

11 ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፣ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ።

12 ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጒሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቍረጥ።

13 ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች።

14 በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፣ ወደምትፈልገው አንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና ልትሸጣት ወይም እንደ ባሪያ ልትቈጥራት አይገባህም።

15 አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፤ አንደኛዋን የሚወዳት፣ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፣ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኵር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፣

16 ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፣ የብኵርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኵር ልጅ ገፎ፣ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ፣ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤

17 ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኵርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኀይል መጀመሪያ ነውና፤ የብኵርና መብት የራሱ ነው።