1 የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ብታየው፣ ወደ እርሱ መልሰህ አምጣለት እንጂ ዝም ብለህ አትለፈው፤
2 ወንድምህ በአቅራቢያህ ባይኖር፣ ወይም የማን መሆኑን የማታውቅ ከሆነ፣ ባለቤቱ ፈልጎት እስኪመጣ ድረስ፣ ወደ ቤትህ ወስደህ ከአንተ ዘንድ አቈየው፤ ከዚያም መልሰህ ስጠው።
3 የወንድምህን አህያ ወይም ልብስ ወይም የጠፋበትን ማናቸውንም ነገር ስታገኝ እንደዚሁ አድርግ፤ በቸልታ አትለፈው።
4 የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታየው፣ በእግሩ እንዲቆምለት ርዳው እንጂ ዐልፈኸው አትሂድ።
5 ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ እንዲህ የሚያደርገውን ሁሉ አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይጸየፈዋልና።