ዘዳግም 22:24-30 NASV

24 ልጃገረዲቱ በከተማ ውስጥ እያለች አስጥሉኝ ብላ ስላልጮኸች፣ ሰውየውም የሌላን ሰው ሚስት አስገድዶ ስለደፈረ፣ ሁለቱንም ወደ ከተማ ደጃፍ ወስዳችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

25 ነገር ግን አንድ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ አግኝቶ በማስገደድ ቢደፍራት፣ ይህን ድርጊት የፈጸመው ሰው፣ ብቻ ይገደል።

26 በልጃገረዲቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉባት፤ ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት ምንም አልሠራችም፤ ይህ ዐይነቱ ጒዳይ፣ አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ከሚገድል ሰው አድራጎት ጋር የሚመሳሰል ነው።

27 ምክንያቱም ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ ስላገኛትና ብትጮኽም እንኳ ለርዳታ የደረሰላት ማንም ሰው ስላልነበር ነው።

28 አንድ ሰው ያልታጨች ልጃገረድ አግኝቶ በማስገደድ ቢደርስባትና ቢጋለጡ፣

29 ሰውየው ለልጅቷ አባት አምሳ ስቅል ብር ይክፈል፤ ልጃገረዲቱን አስገድዶ ደፍሮአታልና እርሷን ማግባት አለበት፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

30 አንድ ሰው የአባቱን ሚስት ማግባት የለበትም፤ የአባቱንም መኝታ አያርክስ።