1 ሙሴና የእስራኤል አለቆች ሕዝቡን እንዲህ ብለው አዘዙ፤ “ዛሬ የማዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤
2 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራ ቅባቸው።
3 የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገር፣ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው።
4 ዮርዳኖስን እንደ ተሻገርህም፣ ዛሬ ባዘዝሁህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ ላይ ትከላቸው፤ በኖራም ቅባቸው።
5 እዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ በድንጋዮቹም ላይ ማናቸውንም የብረት መሣሪያ አታሳርፍባቸው።