ዘዳግም 28:10-16 NASV

10 ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።

11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።

12 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።

13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ መቼውንም ቢሆን እላይ እንጂ ፈጽሞ እታች አትሆንም።

14 ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።

15 ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀ ልቁሃልም፦

16 በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።