ዘዳግም 28:31-37 NASV

31 በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም።

32 ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ፤ በማለትም ዐይኖችህ ሁል ጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ።

33 የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም።

34 የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል።

35 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጒር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቊስል ጒልበትህንና እግርህን ይመታሃል።

36 እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ።

37 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ።