43 በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ።
44 እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።
45 እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስላል ታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም።
46 ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ።
47 በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣
48 በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል።
49 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያሰነሣብሃል፤