ዘዳግም 3:18-24 NASV

18 በዚያን ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ለእናንተ ሰጥቶአችኋል፤ ይሁን እንጂ የአካል ብቃት ያላቸው ሰዎቻችሁ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ፊት በመቅደም መሻገር አለባቸው።

19 ሆኖም ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ፣ (ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁም ስለማውቅ) ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ውስጥ ይቈዩ፤

20 ይኸውም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፋቸውና አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዮርዳኖስ ማዶ የሚሰጣቸውን ምድር እነርሱም እንደዚሁ እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።”

21 በዚያን ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ስል አዘዝሁት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ በገዛ ዓይንህ አይተሃል፤ አሁንም ዐልፈህ በምትሄድባቸው መንግሥታት ላይ ሁሉ እግዚአብሔር ይህንኑ ይደግመዋል።

22 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ራሱ ይዋጋላችኋልና አትፍሯቸው።”

23 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ብዬ ለመንሁት፤

24 “ጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ሆይ፣ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው?