ዘዳግም 3:23-29 NASV

23 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ብዬ ለመንሁት፤

24 “ጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ሆይ፣ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው?

25 አሁንም ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውንያችን መልካሚቱን ምድር፣ ውብ የሆነችውን ኰረብታማ አገርና ሊባኖስን እንዳይ ፍቀድልኝ።”

26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን በእናንተ ሰበብ ተቈጥቶኝ ነበርና አልሰማኝም፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “ይበቃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ስለዚህ ነገር አታንሣብኝ።

27 ወደ ፈስጋ ተራራ ጫፍ ውጣ፤ ወደ ምዕራብና ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅም ተመልከት። አንተ ዮርዳኖስን ስለማትሻገር፣ ምድሪቱን በዐይንህ ብቻ እያት።

28 ነገር ግን ሕዝቡን መርቶ በማሻገር የምታያትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርጋቸው ስለ ሆነ፣ ኢያሱን ላከው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።”

29 ስለዚህ እኛ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ቈየን።