ዘዳግም 30:13-19 NASV

13 ደግሞም፣ “እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ባሕሩን ይሻገራል?” እንዳትልም፣ ከባሕር ማዶ አይደለችም።

14 ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።

15 እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ።

16 አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድ፣ በመንገዱም እንድትሄድና ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን እንድትጠብቅ አዝሃለሁ፤ ከዚያም በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል።

17 ዳሩ ግን ልብህ ወደ ኋላ ቢመለስና ባትታዘዝ፣ ለሌሎች አማልክት ለመስገድ ብትታለልና ብታመልካቸው፣

18 በርግጥ እንደምትጠፉ እኔ በዛሬው ዕለት እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ብዙ አትኖሩባትም።

19 ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤