ዘዳግም 31:10-16 NASV

10 ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፣ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፣ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣

11 እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህበእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ።

12 ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13 ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።

14 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቦአል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ።

15 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።

16 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ።