16 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ።
17 በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን (ኤሎሂም) ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።
18 ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፣ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።
19 “እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ።
20 ወተትና ማር ወደምታፈሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፣ ከበለጸጉም በኋላ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ።
21 ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል። በዘራቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደማልሁላቸው ምድር ሳላስገባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳን አስቀድሜ ዐውቃለሁ።”
22 ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው።