1 ሙሴ ከሞአብ ሜዳ ተነሥቶ ለኢያሪኮ ትይዩ ወደ ሆነው ፈስጋ ጫፍ፣ ወደ ናባው ተራራ ወጣ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሪቱን ሁሉ አሳየው፤ ይኸውም ከገለዓድ እስከ ዳን፣
2 ንፍታሌምን ሁሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ግዛት፣ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፣
3 ኔጌብንና የዘንባባ ከተማ ከሆነችው ከኢያሪኮ ሸለቆ እስከ ዞዓር ያለውን ምድር ሁሉ ነው።
4 ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን “ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፣ ለዘሮቻችሁ እሰጣለሁ’ ብዬ በመሐላ ቃል የገባሁላቸው ምድር ይህች ናት። በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትሻገርም” አለው።
5 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር (ያህዌ) አገልጋይ ሙሴ በሞዓብ ምድር ሞተ።
6 በሞዓብ ምድር በቤተ ፌጎር ፊት ለፊት ባለው ሸለቆ ቀበረው፤ ይሁን እንጂ መቃብሩ የት እንደሆነ እስከ ዛሬ ማንም አያውቅም።