ዘዳግም 4:14-20 NASV

14 ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስ ተምራችሁ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘኝ።

15 እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤

16 ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማናቸውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣

17 ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበር የማናቸውንም ወፍ፣

18 ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል እንዳታደርጉ ነው።

19 ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ፤

20 እናንተን ግን ልክ ዛሬ እንደሆናችሁት ሁሉ ርስቱ ትሆኑለት ዘንድ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እናንተን ከብረት ማቅለጫ ምድጃ፣ ከግብፅ አውጥቶ አመጣችሁ።