ዘዳግም 4:3-9 NASV

3 እግዚአብሔር (ያህዌ) በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል፤

4 አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።

5 ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ።

6 በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።

7 በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?

8 ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?

9 ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው።