11 በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንዳትረሳው ተጠንቀቅ።
12 አለበለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣
13 ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣
14 ልብህ ይታበይና ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣህን አምላክህንእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትረሳለህ።
15 በዚያ ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ በዚያ በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ መራህ፤ ከጽኑ ዐለትም ውሃ አፈለቀልህ።
16 በመጨረሻ መልካም እንዲሆንልህ፣ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን፣ አባቶችህ ፈጽሞ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መገበህ።
17 ምናልባትም፣ “ይህን ሀብት ያፈራሁት በጒልበቴና በእጄ ብርታት ነው” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል።