ዘዳግም 9:18-24 NASV

18 ከዚያም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቊጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በግምባሬ ተደፋሁ።

19 እናንተን ሊያጠፋችሁ ክፉኛ ተቈጥቶ ነበርና፣ እኔም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቊጣና መዓት ፈራሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን እንደ ገና ሰማኝ።

20 እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ለአሮንም ጸለይሁ።

21 ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ አበጅታችሁት የነበረውን ጥጃ ወስጄ፣ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።

22 በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሐታአዋ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አስቈጣችሁት።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከቃዴስ በርኔ ባስ ወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም።

24 እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።