ዘዳግም 9:5-11 NASV

5 ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው።

6 ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሣ አለመሆኑን አስተውል፤ አንተ ዐንገተ ደንዳና ነህና።

7 አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብፅ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፅህ ነህ።

8 በኮሬብ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለቊጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ።

9 እኔም የድንጋይ ጽላቶቹን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን የኪዳን ጽላቶች ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ፣ እህል ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤

10 በእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁበት ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ከተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ትእዛዛት ሁሉ በእነርሱ ላይ ነበሩባቸው።

11 አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ማለትም የኪዳኑን ጽላቶች ሰጠኝ።