ዘፍጥረት 1:19-25 NASV

19 መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን።

20 እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጡራን ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ።

21 በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጡራንን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።

22 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው።

23 መሸ፤ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን።

24 እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ሕያዋን ፍጡራንን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ።

25 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።